ፊንፊኔ #Ethiopia
ጥቅምት 26/2016 (YMN) ከመቶ ሚሊዮን ተሻግሮ ወደፊት እየገሰገሰ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎት መሟላት በራስ አቅም አይቻልም።ይህ ደግሞ የግዴታ ወደ ውጭ እንድናማትር ያስገድደናል።በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉንም ፍላጎቶች በራስ አቅም መተካት ካልተቻለ ደግሞ እስካሁን እያደረግነው እንዳለው ወደብ ተከራይተን ከፍተኛ ወጪ እያወጣን ማስገባት ሊኖርብን ነው።ይህ ደግሞ በሚከተሉት ምክንያቶች በዘላቂነት አያዋጣንም።
የንግድ መስመሮች
ኢትዮጵያ ወደብ የሌላት ሀገር በመሆኗ ብቻ ከሶስት አስርት ዓመታት ለዘለቀ ከፍተኛ ወደብ አገልግሎት ወጪ ሲያጋጥማት ቆይቷል።ይህ ብቻ ሳይሆን ለወጪና ለገቢ የንግድ መስመሮች በጎረቤት ሀገሮች ጥገኛ እንድትሆን አስገድዷታል።የመርከብ መንገዶችን እና ወደቦችን በቀላሉ ማግኘት ካልተቻለ ዕቃዎችን ማጓጓዝ የበለጠ ውድ እና ጊዜ የሚወስድ ጉዳይ ነው።ይህ ደግሞ የንግድ ሥራ ወጪን ከፍ ከማድረጉም በላይ የኢኮኖሚያዊ እድገቶችን፣ እድሎችን እየገደበ ይገኛል። የዚህን ውጤት በቀጥታም እያንዳንዱ ዜጋ ላይ በየጊዜው እንመለከተዋለን።
ምርትን የማስመጣት እና የወጪ ንግድ የሚያሳልጠው ወደብ አለመኖር (import, export goods) የጎረቤት ሀገራት ጥገኛ ከማድረጉና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከመጠየቁ ባሻገር ወደብ የሌላት ኢትዮጵያ አየር ወይም ባቡር ባሉ ውድ የመጓጓዣ ዘዴዎች ላይ ብቻ እንድትተማመን እያስገደዳት ይገኛል።ይህ ደግሞ የንግድ ሥራ ወጪን ከፍ በማድረጉ ምክንያት የኢኮኖሚያዊ እድገትን እየገደበ ነው።ዓለም ላይ ካለው ያልተረጋጋ የዋጋ ትመናና ማሻቀብ ጋር የእነዚህ ወጪዎች መደራረብ ሲጨመር አሁን እየተፈጠረ ላለው ኢኮኖሚያዊ ውጥንቅጥ ምክንያት ይሆናል።
ኢትዮጵያ ቀጥተኛ የወደብ ተጠቃሚ ባለመሆኗ ምክንያት የኢኮኖሚና የልማት እድገት ላይ የሚፈጥረው ችግር ከላይ ያነሳሁት ብቻ አይደለም።ከእርሱ በተጨማሪ የኢትዮጵያ የወደብ ተጋሪ አለመሆን በዓለም አቀፍ ንግድ ውስጥ ለመሰማራት እና ዓለም አቀፍ ገበያዎችን ለመድረስ ፈተናዎች እየጋረጠባት ይገኛል።
ለዓለም አቀፍ ንግድ ያለን ተደራሽነት ውስን ከመሆኑም በላይ የንግድ ሸሪክ ሀገሮችና ታላላቅ ካምፓኒዎች ጋር እንዳንወዳጅ እድሉን አጥብቦብናል።የባህር ላይ ቀጥተኛ መዳረሻ ስለሌለ ኢትዮጵያውያን ራቅ ካሉ ሀገሮች ጋር አዲስ የንግድ ግንኙነት ለመመስረት ውስብስብ መስመሮችንና አስቸጋሪ መንገዶችን የግዴታ መከተል ይኖርብናል።
መዛግብት እንደሚያስረዱን የባህር ንግድ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ወደቦች በሀገሮች ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገት ውስጥ ማዕከላዊ ሚና ይጫወታሉ።ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የዓለም የሸቀጥ ንግድ (በመጠን) የሚጓጓዘው በባህር መንገዶች ነው።በኮንቴይነር የሚጓጓዙ ምርቶች ማረፊያ ደግሞ ወደቦች (የባህር በር) ናቸው።ለልዩ ልዩ ፍላጎቶች የሚውሉ እነዚህ ቁሶች ደህንነታቸው ተጠብቆና ጥራታቸው ሳይጓደል ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የኢትዮጵያ መንግሥት በነፃነት ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆን ይገባዋል።
በተመሳሳይ በሀገር ውስጥ ተመርተው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በወደብ እንቅስቃሴ ላይ የሚኖረውን የጥራት ሂደት መከታተል ያስፈልጋል። ይሁን እንጂ ሀገሪቱ ወደብ አልባ (landlocked) በመሆኗ ምክንያት ፍላጎታችንን ለማስፈፀም ውስብስብ ሂደቶችን የግዴታ መከተል ይኖርብናል።
ወደብ አልባ መሆን የሀገርን አማካይ እድገት በ1 ነጥብ 5 በመቶ ድረስ (አሃዙ በጥናቶች ላይ የተለያየ ቢሆንም) በዓመት እንደሚቀንስ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ውጤታማ ያልሆኑ የወደቦች አገልግሎቶችንና የእቃ ማጓጓዝ ሂደቶች አሰራር በማዘግየት አቅምን ይቀንሳሉ።ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነን መንግሥት የሀገር ውስጥ ፍላጎቶችን በግዥ ለማስገባት በሚሞክርበት ጊዜ በቢሮክራሲና በልዩ ልዩ ምክንያቶች ወደብ ላይ ተቀምጠው ረጅም ጊዜ የሚቆዩ ምርቶች (እንደ ማዳበሪያ፣ ስንዴና ሌሎችም ሸቀጦች) ስንመለከት ነው።ወደ ውጭ የሚላኩትም ቢሆኑ ወደብ ላይ በመቆየታቸውና ጥራታቸው (export standard) በመጓደሉ ምክንያት ለኪሳራ መዳረጋቸው አይቀርም።
ወደብ ቢኖረን......
ደብ ቢኖረን…የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ኢትዮጵያ የወደብ ባለቤት ብትሆን (አፈፃፀሙንና የህግ ሂደቱን ለጊዜው እንተወውና) አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጠረ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ጫና በግማሽ እንደምትቀንስ ያምናል።ወደብ በትክክል ከተሰራና ከተመራ በምርት እና ሥርጭት ሥርዓቶች ላይ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ የማኑፋክቸሪንግ፣ የሎጂስቲክስ እድገትን ለመደገፍ፣ የሥራ እድል ለመፍጠር እና የገቢ አማራጮችን ለማስፋት ያግዛል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ እንደ አለመታደል ሆኖ የባህር በር ከሌላቸው ታዳጊ ሀገራት ተርታ የምትመደብ መሆኑና የባህር ወደብ ባለመኖሩ ብዙ ዋጋ እየከፈለች ነው።ዜጎቿ በዚህ ምክንያት ብዙ እድል አጥተዋል። የንግድ ህልውናችን የሚወሰነው በሌሎች ሀገሮች ወደብ ላይ ነው። የመጓጓዣ አገናኝ የግብይት ወጪዎች ከፍ ያለ በመሆኑ እቅሙን ለተጨማሪ ልማትና ኢንቨስትመንት እንዳይውል ተገድደናል።
ወደብ ቢኖረን በዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ አስፈላጊ አንጓዎች የምንላቸውን ሸቀጦችን የሚይዙ የኮንቴይነሮችንና ልዩ ልዩ የወደብ አገልግሎቶችን በቀላሉ በትንሽ ወጪ መቆጣጠር ያስችለናል። በተለይ ለኢኮኖሚ ዲፕሎማሲና ለንግድ ሽርክና የድርድር አቅምን የሚያሳድገው ወደብ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ወደቦች ለብዙ ታዳጊ ኢኮኖሚዎች “የእድገት ስትራቴጂ” ተደርገው ይወሰዳሉ፤ ወሳኝም ናቸው።
ከፍተኛ ጥራት ያለው የወደብ መሠረተ ልማት ዝርጋታ ቢኖረንና በብቃት የሚሰራ ቢሆን ለእድገት ስትራቴጂዎች ተፈፃሚነት በተለይም የወጪ ንግድ ገበያውን ለመምራት ድርሻው የላ ቀ ይሆናል።
እንደ መውጫ
እኛ ኢትዮጵያውያን በኢኮኖሚው ረገድ ፈቀቅ እንድንል፤ የልማት አጀንዳዎቻችንን በተገቢው ለማስፈፀም ቀጥተኛ የወደብ ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባን ማመን ይኖርብናል። “እንዴት እናስፈፅመው” የሚለውን ለሕዝብ ውይይት፣ ለዓለም አቀፍ ሕጎችና ለወከልነው መንግሥት በኃላፊነት እንተወው። በመሠረታዊነት ግን “ወደብ የአንድ ሰሞን የፖለቲካ አጀንዳችን ሳይሆን የህልውና ጉዳያችን” መሆኑን በአግባቡ መረዳት ይኖርብናል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ይህንን ጉዳይ ወደ መድረክ አምጥቶ የመወያያ ርዕስ ማድረጉን እናስታውሳለን። ጉዳዩን በሚገባ ካለማጤን አሊያም በስሜታዊነት ተነሳስተን ሰሞነኛ አጀንዳ ብቻ እንደሆነ ማሰባችን ግን የዚህ ርዕሰ ነገር ፀሐፊ አያምንበትም።
አጀንዳውን ያንሸራሸረውም ይሁን ጉዳዩን አንሸዋርሮ የተረዳው አካል አንድ ቁልፍ የሆነ ጉዳይ ማወቅ ያለበት የባህር በር ባለቤት መሆን ለዛሬ ሳይሆን ለነገ የኢትዮጵያ ህልውና መሠረት ነው። ለዚህ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ዛሬ ላይ ባናስፈፅመውም እስክናሳካው ድረስ አጀንዳችን ሆኖ ልንወያይበት ይገባል” ማለታቸው። ሰላም!!
ምንጭ:-
አዲስ ዘመን
0 Comments