የንግድ ስርዓታችን ህመም በአግባቡ ይታከም!



ፊንፊኔ #Ethiopia ጥቅምት 28/2016(YMN) እንደ አገር የንግድ ዘርፉ በሽተኛ ሆኗል በህመም ላይ ይገኛል፣ንግዱ መታመሙን ሁሉም ያውቃል ከማወቅም አልፈን አሁን ተላምደነዋል

የፈረደበት ስግብግብ ምንለው ነጋዴ ይህቺን የመላመድ ባህሪያችን ተረድቷታል በደንብ ያውቃታል፤የሃምሳውን ብር መቶ፤የአንድ ሺውን ሁለት ሺህ ብር ብሎ ቢሸጥ ማን ከልካይ አለው?

በነገራችን ላይ ይህቺን ነገር እንደ እኔ ታዝባችሁ ይሆን?በአገራችን ውስጥ መቼም ቢሆን የአንድ ምርት ዋጋ በአንድ ወቅት ከፍ ካለ ወይም ከጨመረ በቀጣይ የምርቱ መጨመርና መትረፍረፍ ቢኖር እንኳ ወደ ቀደሞ የመሸጫ ዋጋ የሚመለስበት ወይም ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ የሚሸጥበትና መገበያየት የሚቻልበት ሁኔታ አይታይም እንዲያውም ፈፅሞ የለም ለምን ይሆን?እንጠይቅ!የነፃ ገበያው ስርዓት እንዲህ ነው እንዴ?ነጋዴው ነፃ ገበያ ስለሆነ በፈለኩት ዋጋ የመሸጥ መብት አለኝ ይላል፤ልክ የዘመኑ ልጆች መብቴ ነው እንደሚሉት ዓይነት

ኧረ ለመሆኑ የአገራችን የንግድ እንቅስቀሴ ህመም ዋነኛ ምክንያት ምንድነው ትላላችሁ? ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን የዓለም ሁኔታን አጣቅሰው አልፎ አልፎ ከሚነግሩን ውጭ በቀጥታ ተጨባጭ ምላሽ ሊሰጠን የሚችልና አቅም ያለው የንግድ ዘርፉ አካል አለ ወይ? አለ የተባለው የንግድ ዘርፍ የመንግስት አካል ችግሩ ምንድነው?ይኼ ንግድና ቀጠናዊ ትስስር የተባለው ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በሕይወት አለ እንዴ?እንዴት ነው ባያሌው? ብለን ወጋ ወጋ እናድርገው እንጂ! የምን ዝም ነው?

ዝም ባለ አፍ ዝምብ አይገባምብለው አስተምረውን ዝም ብለን ተቸገርን እኮ!ይህ ከላይ በስም የጠቀስኩት የመንግስት ተቋምና በስሩ የሚገኙ መዋቅሮቹ ለምን እና ለማን እንደሚሰሩ የሚያውቁ አይመስልም

መንግስት ይሰሩልኛል ሕዝቤን ያገለግላሉ ብሎ እምነት ጥሎባቸው በቦታው ላይ ያስቀመጣቸው ባለስልጣናትና የበታች የዘርፉ የስራ ኃላፊዎች ራሱን መንግስትን ሲያስወቅሱ እንዴት ዝም ይባላል?ገበያ የማረጋጋት ስራዎችን ዘላቂ መፍትሄ በሚገኝበት መልኩ ለምን መስራት አልቻሉም?ለመሆኑ የንግድ ስርአቱን ስብራትና ህመም ለማከም ሞክረዋል?ወይስ እዚያው የፈረደበት መስሪያ ቤት ገብተው ውለው ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ?

እነዚህ የንግዱ ዘርፍ ሰዎች ሚዲያን እንደ ጦር ይፈራሉ አሉ ምን ያስፈራቸዋል? ለሕዝብ ጥያቄና ቅሬታ ምላሽ ስጡ ተብለው ሲጠየቁ ምክንያት የሚያበዙ ሲያሻቸውም በማን አለብኝነት እምቢ የሚሉ መሆናቸው ተስተውሏል

ለነገሩ ምን ሰርተው መናገር ይችላሉ?የሰራና እኔ የሕዝብ አገልጋይ ነኝ ብሎ የሚያምን የመንግስት አካል ስላከናወነው ስራ ፊትለፊት ወጥቶ በድፍረት ለመናገርና ህብረተሰቡን ለማስረዳት አይቸገርም፤ደረቱን ነፍቶ ለሕዝብ የሰራውን ስራ በዝርዝር ያስረዳል ከዚያም ሕዝብ ያጨበጭብለታል ባያጨበጭብለትም ተረድቶ ይታገሳዋል

የንግድ ስርዓቱ ህመም የሚጀምረው ከዘርፉ አመራር ነው፤ማሳያው ውጤት አልባ ሆኖ የህዝብ ቅሬታ ምንጭ መሆኑ ነው አመራሩና በየደረጃው ያለው የስራ `ሃለፊዎች በእኔነት ስሜት ቢሰሩ ኖሮ አሁን ያለው ውጥንቅጥ ሊፈጠር አይችልም

የነዳጅ ምርቶች በዓለም አቀፍ ዋጋ ትመና ምክንያት ቢቀያየር በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችና አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል የሚጠቀምባቸው ሸቀጦችና የፍጆታ ምርቶች ዋጋ እንደ ነጋዴውና ደላላው ፍለጎት ዋጋቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲጨምር ልጓም ማበጀት ያለበት የንግድ ስርዓቱን የሚመራው የመንግስት አካል ነው

የንግድ ዘርፉ እንቅስቃሴ ዜጎች የሚዘረፉበት፤አምራቹ የልፋቱን ዋጋ የማያገኝበት፤ደላላውና ቀማኛው በኔት ወርክ አማካኝነት የሚጠቃቀምበትና የሚከብርበት ሆኗል ህመሙ ከፍ ያለ ነው የሚፈወስበት መድሃኒት እንዲገኝለት እንመኛለን

Post a Comment

0 Comments