ፊንፊኔ #Ethiopia ታህሳስ 03/2016(YMN) ከህግ አውጭው፣ ከህግ ተርጓሚው እና ህግ አስፈፃሚው ቀጥሎ እንደ አራተኛ መንግስት የሚጠቀሰው ሚዲያ አገራትን በዓለም ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ እስከማድረግ ደርሷል። በሌላ በኩል ደግሞ ሚዲያን መግራትና በአግባቡ መጠቀም ያልቻሉ አገራት ፈራርሰዋል።
ሚዲያዎችን ሀሳቦች በነፃነት የሚንሸራሸሩባቸው በማድረግ በጅምር ላይ ላለው አገረ መንግስት ግንባታችን ቁልፍ ሚናቸውን እንዲወጡ በተለይም ከለውጡ ጀምሮ አበረታች ስራዎች ተከናውነዋል።
የህዝብ ሀብት የሆኑ ሚዲያዎች ሪፎርሞች ላይ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን ጭምር የቦርድ አባላት በማድረግ አካታች እርብርብ ተጀምሯል።
ከሚዲያ ነፃነት ጎን ለጎን የሚዲያ ተጠያቂነትም መኖሩን የሚዘነጉ አካላት የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ እኩይ ዓላማቸውን ለማስፈፀም በማዋል ህዝባችን ላይ መከፋፈልን የሚሰብኩ የጥላቻ መልዕክቶቻቸውን በስፋት ማስተላለፋቸውና አሁንም የሚያስተላልፉ መኖራቸው ከህዝባችን የተደበቀ አይደለም።
ብሔርን ከብሔር አገርን ከአገር ለማጋጨት የሚዘሩ የጥላቻ ንግግሮችን የሚያመርቱ አካላትን በህግ አግባብ ተጠያቂ ማድረግ የመንግስት ሀላፊነት ቢሆንም ሁሉም ዜጋ የጥላቻ ንግግሮችን ለማረም የተዘረጉ የጥቆማ ስርዓቶችን በአግባቡ መጠቀም ይገባዋል።
ሁላችንም ለምናስተላልፋቸው መልዕክቶች መጠንቀቅና ሀላፊነት መውሰድም ግድ ይለናል።
ሚዲያዎቻችንን ከዕዳ ወደ ምንዳ የምንቀይረው አገር አፍራሽ መልዕክቶችን ሁላችንም ባልሰማ በማለፍ ሳይሆን በማጋለጥ እውነቱን ስናሰርፅ መሆኑን መረዳት ይገባል።
ሀሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካላት በድርጊታቸው ሳይሸማቀቁ ውሸትን ለማጋለጥና እውነታውን ለማሳወቅ ትችትን በመፍራትና በዓላማ ባለመፅናት ወደ ኋላ ማለት አይገባም።
የአዲሱን ሚዲያ አብዮት ወደ ጎን በማለት ሳይሆን በመግራት ለአገር ጠቃሚ ሀሳቦችን በማስተላለፍ አገረ መንግስት ግንባታችንን ማጠናከር ወቅቱ የሚጠይቀው ተልዕኮ ነው።
በስልኮቻችን ሚዲያዎችን ይዘን የምንጓዝበት ዘመን ላይ በመድረሳችን ጊዜውን በሚመጥን መልኩ መቃኘትና መጠቀም ይገባል።
በምናስተላልፈው መልዕክት፣ በምናስተላልፍበት ሚዲያ እና በተከታያችን መካከል የሚፈጠሩ የኮሙኒኬሽን ተግዳሮቶችን በመቅረፍ የጥፋት ሳይሆን የልማት ስራዎች በስፋት እየተሰራጩ ሚዲያ ለአገር ግንባታው የድርሻውን እንዲወጣ መትጋት ከእየአንዳንዳችን ይጠበቃል።
የሴራ ፖለቲካ ምህዳሩን ወደ ፉክክርና ትብብር ለመውሰድ የምናደርገውን ጥረት ለማጠናከር አንድ በሚያደርጉን አገራዊ ጉዳዮች ሁላችንም ታሪካዊ አሻራችንን ለማሳረፍ የሚያግዙ አቀራራቢና አሰባሳቢ ጥረቶች በመደረጋቸው አብሮ የመስራት ባህላችን ላይ መሻሻሎች ታይተዋል።
ሊያራርቁን የሚችሉ ተገዳዳሪ እና የአገረ መንግስት ግንባታችን አደጋ ላይ የሚጥሉ ነጠላ ትርክቶችን ለመግራት እና በምትኩ አብሮነታችንን የሚያጠናክሩ፣ የአገረ መንግስት ስራዎቻችንም የሚያፋጥኑ የወል ትርክቶችን ለመገንባትም ብርቱ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል።
የተቀናጀና በዲሲፕሊን የሚመራ አመራርና ስርዓት ለመገንባት እንዲሁም የፓርቲያችን አገር አሻጋሪ አሸናፊ እሳቤዎች ወደ ተግባር በመለወጥ የህዝባችንን ህይወት ለማሻሻልና ሁለንተናዊ ብልፅግናችንን ለማረጋገጥ የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂዎቻችንን በአግባቡ መምራት አንዱ የትኩረት አቅጣጫችን ነው።
ምንጭ: የብልጽግና ፓርቲ ፌስ ቡክ ገጽ
0 Comments