የህብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ሳንካዎችን እናርም!



ፊንፊኔ #Ethiopia ሕዳር 30/2016(YMN) ብዝሀነትን ለማስተናገድ የሚያስችል ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማፅናትና መገንባት የህብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ሳንካዎችን ለማረም ቀዳሚው እርምጃ ነው።
ህብረ-ብሄራዊነት በሰፈነባቸው ኢትዮጵያን በመሳሰሉ ሀገራት የፌዴራሊዝም አስተሳሰብና አደረጃጀት ትክክለኛው እና ዘላቂው መፍትሄ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡
የፌዴራሊዝም ስርዓት ከዴሞክራሲ መስፋትና ከዴሞክራሲ አስቻይ ሁኔታ መፅናት ተነጥሎ ሊታይም አይችልም፡፡
የሀገራችን ብዝሀነት የልማትና የብልፅግና መሳሪያ ካልተደረገ ሰላምን፣ መልካም ግንኝነቶችን እንዲሁም ሀገራዊ አንድነትን ማስጠበቅ አይቻልም፡፡
ህብረ-ብሔራዊ ማንነቶቻችን ውበቶቻችን እና ሀብቶቻችን መሆናቸውን በመገንዘብ ማልማትና የብልፅግናችን ሞተር ማድረግ ይገባል።
በብዝሀነት አያያዝ የሚታዩ ጉድለቶችን ለማስወገድ ፓርቲያችን ህብረ-ብሄራዊነትን የተላበሰ አስፈፃሚ እንዲገነባ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ሲሆን እንደ መንግስትም በየደረጃው በሚገኙ የአስፈፃሚ አካላት መዋቅሮች የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ጭምር በማሳተፍ በአገራችን ታሪክ ያልነበሩ መልካም ጅምሮች አሉ።
አሁን በስራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀር ስርአት ከነጉድለቱም ቢሆን ብዝሀነትን ለማስተናገድ አስችሏል፡፡ የሞግዚት አስተዳደርን በማስቀረት ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን አረጋግጧል፡፡ ይህም ህብረብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ተጋርጦብን የነበረውን የውስጥና የውጭ ፈተና በማሻገር የሀገራችንን ህልውና ለማረጋገጥ አስችሏል፡፡
ከለውጡ በፊት በነበረው የፌዴራሊዝም አተገባበር ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ላይ ከነበረው ሰፊ ክፍተት በተጨማሪ የዴሞክራሲ እጦት እና ሰብአዊ መብት ጥሰት፣ የቋንቋ ብዝሀነትን በማስተናገድም ጉድለት የነበረበትና ብሄራዊ መግባባትንም ማረጋገጥ ያልቻለ ነበር፡፡
ከለውጡ በኋላ እነዚህን ጉድለቶች በማስተካከል እውነተኛ ህብረ-ብሄራዊ ፌደራሊዝምን ለመገንባት ሪፎርሞችን በማድረግ መሰረታዊ ለውጦች መመዝገብ ጀምረዋል፡፡
በአገራዊ ጉዳይ አንዱን ልጅ አንዱን የእንጀራ ልጅ፣ አንዱን አድራጊ ፈጣሪ አንዱን በሞግዚት የሚተዳደር የሚያደርግ ሳይሆን እውነተኛ ህብረ-ብሄራዊ ፌደራሊዝም መገንባት የሚያስችል መደላድል መፍጠር ወሳኝ መሆኑ ስለታመነበት ከለውጡ በኋላ በተወሰዱ እርምጃዎች ባይተዋር የነበሩ አካባቢዎችን ጭምር በሁሉም መስክ ፍትሀዊ ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግ መጀመሩ የማይታበል ሀቅ ነው።
ከህብረ-ብሔራዊ ተፈጥሯችን በሚጣረስ መልኩ የግለሰቦችንና የቡድኖችን ፖለቲካዊ ፍላጎቶች ለማሟላት ሲባል የብሄር ካባ በመልበስ ፅንፈኝነትን ማራመድና ማስፋፋት መነሻውም መዳረሻውም ጥፋት በመሆኑ አስተሳሰቡም ተግባሩም በብልፅግና ጉዟችን ላይ የደቀነውን አደጋ በጋራ መመከትና ማረም ከሁላችንም ይጠበቃል።
ፅንፈኝነትን በመዋጋት አሸናፊውና በህዝባችን ዘንድ ተቀባይነት ያገኘው ሀሳብ የበላይነት እንዲኖረው መስራት የህዝባችንን ፍላጎት ማሟላት ነው።
የፅንፈኝነት አስተሳሰብ ሊወገድ የሚችለው በሁሉም የትግል ሜዳዎች መሆኑን በመገንዘብ በየዘርፉ የጀመርናቸውን ስኬታማ ጥረቶች አጠናክሮ መቀጠል እንጅ ችግሮችን የፀጥታ ችግር ብቻ አድርጎ መውሰድም አግባብ አይደለም።
ማንኛውም በየደረጃው የሚገኘው ፈፃሚና አስፈፃሚ እንዲሁም የፓርቲ መዋቅራችን ከብሄር አክራሪነት እና ፅንፈኝነት አስተሳሰብ ራሱን ነፃ በማድረግ በሌሎች የሚታዩ የፅንፈኝነት አስተሳሰቦችንና ዝንባሌዎችን በግንባር ቀደምነት በፅናት መታገል ይገባዋል፡፡
ሚዲያዎች እና ኪነ-ጥበብም የሀገራችንና የህዝባችንን ጥቅም የሚጎዱ አስተሳሰቦች እንዲታረሙ፣ የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አስተሳሰቦች የበላይነት እንዲያገኙ የማይተካ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል።
መንግስትም ህብረ-ብሄራዊ ፌዴራሊዝም እንዲጎለብትና ዴሞክራሲያዊነት እንዲዳብር የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሀላፊነቱን በአግባቡ በመወጣት አገራዊ አንድነትን ማስጠበቅ ግድ ስለሚለው ህዝባችንን ባሳተፈ መልኩ የሚደረገው የፀረ-ፅንፈኝነት ትግል ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ከፋፋይ የተናጠል ትርክቶችን በማረም የወል ትርክቶችን የመገንባቱ እንቅስቃሴም ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር የሚደረገው የፀረ-ፅንፈኝነት ትግሉ አካል ነው።
ስትራቴጅዎችን በመንደፍ ብዝሀነትን በብቃትና በፍትሀዊነት የሚመራ፣ የህዝብ አገልጋይነት ስሜትን የተላበሰ፣ በአመለካከትና በተግባር የተቀናጀ አመራርነትም ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የጎላ ሚና እንዳለው በማመን የአመራራችንን አቅም ለማጎልበትና ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ተከታታይነት ያላቸው ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ልብ ይሏል፤ ከዕዳ ወደ ምንዳ በሚል ርዕስ ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለመጡ የመንግስት አመራሮች እስከ አራተኛ ዙር የተሰጠውን የአቅም ግንባታ እና የወንድማማችነት እህትማማችነት ማጠናከሪያ ስልጠና ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።
ምንጭ: በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ/ፅ/ቤት

Post a Comment

0 Comments