ቅንነትንና ብቃትን የተላበሰ አገልግሎት ለህዝባችን ተጠቃሚነት!




ፊንፊኔ ታህሳስ 23/2016(YMN) የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ በአገራችን የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለው ቢሆንም ዘመኑን በሚመጥን መልኩ ባለመዘመኑ የችግር ፈችነት ሳይሆን የችግር ፈጣሪነት ምስል ሸፍኖት ቆይቷል ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ተገልጋዩ ጊዜውን፣ ሀብቱን እና ጉልበቱን ሳያባክን ጉዳዩን አስፈፅሞ እሱም በተራው ወደ ተሰማራበት የስራ መስክ በፍጥነት ለመመለስ ሲያስብ በህሊናው የሚደቀነው እንደ ራስዳሽን ተራራ መውጣት እና እንደ ዳሉል ዝቅተኛ ቦታዎች መውረድ የሚጠይቀው፣ መሰናክሎች የበዙበት፣ ጠመዝማዛው የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ነው።
በመንግስት ተቋማት የሚስተዋለው የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር በአገራችን ከሚስተዋሉ ስር የሰደዱ ችግሮች ዋናው መሆኑን በመረዳት በፓርቲያችን የሚመራው የለውጡ መንግስት ሁሉም ተቋማት ምቹ የስራ አካባቢ እንዲፈጥሩ ማድረግን ጨምሮ በርካታ አበረታች እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም የጠ/ሚ ዶ/ር ዐብይ አህመድን አርአያነት ተከትሎ ከንቲባ ፅ/ቤትን ጨምሮ ሁሉም ተቋማት ቢሯቸውን በማደስና በማስዋብ እንዲሁም አስፈላጊ ግብአቶችን በማሟላት ለሰራተኞቻቸው እና ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ምቹ አካባቢን እንዲፈጥሩ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው፤ በዚህም አንዳንድ ተቋማት ለከተማችን ውበትም ተጨማሪ ድምቀት እስከመሆን ደርሰዋል።
ተቋማት አገልግሎት አሰጣጡ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ህጎችን፣ ደንቦችን፣ መመሪያዎችን እና አሰራሮችን በመፈተሽ አሳሪዎችን አሰሪ በማድረግ ወደ ፊት መራመድ ጀምረዋል።
ተገልጋዩ ብሔሩ፣ ሀይማኖቱ፣ ፆታው፣ የፖለቲካ አመለካከቱ፣ የስጋ ዝምድናው እና መሰል አግላይ አስተሳሰቦች ግምት ውስጥ ሳይገቡ ፍትሀዊና ቀልጣፋ አገልግሎት የማግኘት ህገ-መንግስታዊ፣ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አሉት።
"ደንበኛ ንጉስ ነው" የሚለው ድንቅ አባባል የተወሰኑ ተቋሞችን ተገልጋይ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ተገልጋዮች የሚወክል ነው። በሁሉም ተቋሞች የሚገኝ ሁሉም አመራር እና ባለሙያ የህዝብ አገልጋይ መሆኑ ላይ የጠራ አቋም ሊኖረው ይገባል። ግለሰቦች ብቻም ሳይሆኑ ፓርቲያችን ብልፅግናም አምስት ዓመታት ህዝባችንን ለማገልገል ከህዝባችን ይሁንታን ያገኘ የህዝብ አገልጋይ ፓርቲ ነው።
ፓርቲያችን ብልፅግና ነፃ፣ ገለልተኛ እና አካታች ሲቪል ሰርቪስ እንዲገነባ አቅጣጫዎችን ቀይሶ ተግባራዊነታቸውን በልዩ ትኩረት እየተከታተለ ይገኛል።
አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን የህዝባችንን መጉላላት ለማስቀረት፣ የጊዜ፣ የጉልበት እና የሀብት ብክነትንም ለመቅረፍ በከተማችን የሚገኙ ተቋማት የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ፈጣን መሻሻል እያሳየ መሆኑን የጤና እና የመሬት ተቋማት እንዲሁም የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪዎች አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻልን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።
አመራሩም ሰራተኛውም በቅንነትና በቅንጅት በተረባረበባቸው ዘርፎች አመርቂ ውጤቶች መመዝገብ መጀመራቸውን ህዝባችን ይመሰክራል፤ ዓለም አቀፍ እውቅናዎችም ተችረውናል።
ሰሞኑን በከተማ አስተዳደሩ የተጀመረው የሲቪል ሰርቫንቱ ምዘናም ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት አሰጣጥ ለመፍጠር የተጀመረውን ጥረት ማጠናከር፣ በዘርፉ የሚስተዋለውን በአንድ በኩል የሰው ሀይል እጥረት በሌላ በኩል ደግሞ የሰው ሀይል ብክነትን በማስተካከል በሁሉም መስክ ፍትሀዊነትን ለማስፈንና የህዝባችንን ተጠቃሚነት ማረጋገጥን ዓላማው ያደረገ መሆኑን ልብ ይሏል።
ቅንነትን በመላበስ፣ እውቀትና ክህሎታቸውን በማሳደግ ግለሰቦች አገልግሎት አሰጣጡ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የማይተካ ሚና ቢኖራቸውም የማይዋዥቅ አገልግሎት አሰጣጥ ለመስጠት፣ በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ጉድለቶችንም በዘላቂነት ለማረም ቁልፉ ተቋም ግንባታ መሆኑን ማስመር ይገባል።
ታታሪዎች የሚበረታቱበትና የሚበራከቱበት፣ ደካሞች ደግሞ የሚደገፉበት፣ አጥፊዎችም የሚታረሙበት ግልፀኝነት ያለው አሰራርና ስርዓት በመዘርጋት ቅንጅታዊ ርብርብ የማድረጉ ጉዳይም ልዩ ትኩረት ይፈልጋል።
ብቃትንና ውጤታማነትን ከብዝሀነትና አካታችነት ጋር በማጣጣም በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በመቅረፍ የህዝባችንን እርካታ ለማሳደግ ለተጀመረው ሪፎርም ስኬታማነት እንረባረብ!
ምንጭ: በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት

Post a Comment

0 Comments