ፊንፊኔ ታህሳስ 24/2016(YMN) በኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ መካከል የተፈረመው ስምምነት ሶማሊላንድን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሊዙ የሚታሰብ ድርሻ እንዲኖራት ያስችላል ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡
አገልግሎቱ የስምምነት ሠነዱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ÷ የተፈረውም ስምምነት ሁሉን አቀፍ የትብብርና አጋርነት የመግባቢያ ሰነድ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ወታደራዊ መስኮች ሰፋ ያሉ የትብብር አድማሶችን ያካተተ ነው ብሏል።
ስምምነቱ የኢትዮጵያውያንን የዘመናት ጭንቀትና ቁዘማ ለማከም የሚያስችል አጋጣሚን የፈጠረ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
በኢፌዴሪ እና ሶማሊላንድ መካከል ሁሉን አቀፍ የትብብርና አጋርነት የመግባቢያ ሰነድ ተፈርሟል፡፡
ስምምነቱ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ወታደራዊ መስኮች ሰፋ ያሉ የትብብር አድማሶችን ያካተተ ነው።
ሶማሊላንድ የአፍሪካ ቅርምትን ተከትሎ በእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ሥር የቆየች ሲሆን በፈረንጆቹ ሰኔ 26 ቀን 1960 ነጻነቷን አግኝታለች። በወቅቱ በርካታ ሀገራት እውቅና ሰጥተዋት እንደነበርም ይታወሳል።
ሆኖም በዚያው ዓመት ከአምስት ቀናት በኋላ በጣሊያን ቅኝ ግዛት ቆይታ ነፃ ከወጣችው ሞቃድሾ ጋር በፈቃዷ ተቀላቅላለች።
በፈረንጆቹ 1991 ዳግም ነጻነቷን አውጃ በተከታታይ ሰላማዊ ምርጫ ሰከን ያለ የመንግሥት ቅይይር በማካሄድ ለ30 ዓመታት ዴሞክራሲን በመለማመድ ላይ ትገኛለች። ሀገራችንን ጨምሮ አንዳንድ ሀገራት በሐርጌሳ ቆንስላ ጽ/ቤት ከፍተውም ይንቀሳቀሳሉ።
ነገር ግን እስካሁን የተሟላ ዕውቅና አላገኘችም። ይህም ሆኖ የወደብ አገልግሎትና ልማትን ጨምሮ ከአንዳንድ ሀገራት ጋር ስምምነት ፈርማለች።
ከዚህ ቀደም በርበራ ላይ ለኢትዮጵያ የ19 በመቶ ድርሻ እንዲኖራት ይፈቀድ የነበረ የመግባቢያ ሰነድ ተፈርሞ እንደነበርም ይታወሳል። በአሁኑ ወቅት ሌሎች ሀገራት ተመሳሳይ ሂደት እየተከተሉ መሆኑም ይታወቃል። ይሄ ሲሆን የተሰማ ኮሽታም ሆነ ቅሬታ አልነበረም።
ኢትዮጵያ የወታደራዊ ቤዝና ኮሜርሻል ማሪታይም አገልግሎት በሰጥቶ መቀበልና በኪራይ ለማግኘት የተፈራረመችው የመግባቢያ ሰነድና ሂደትም በመሠረቱ አንድና ያው ነው።
በሀገራችንና በሶማሊላንድ መካከል ቆየት ያለ የትብብር ስምምነት ነበረ። ሁለቱ ወገኖች ወዳጅነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር ባደረጉት ጥረት የተገኘው የአሁኑ ሁሉን አቀፍ ትብብርና አጋርነት ሰነድ የሁለቱንም ወገኖች ታሪካዊ የሚባሉ ጥያቄዎችን በሚመልስ፣ ዝርዝር ፣ግልጽና ስትራቴጂክ አጋርነትን በዘላቂነት ለመገንባት የሚያስችል ነው።
በሶማሊላንድ በኩል ማንም አገር እየፈለገ ሊከውናቸው የማይችሉ ጥያቄዎቻቸውን የሚመልስ ሲሆን ከማንም ሀገር ሊያገኙት የማይችሉትን እገዛና ሽርክና ያጎናጽፋቸዋል።
የሀገራችንን መሻቶች በተመለከተ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን በግልጽ እንደሰፈረው ለጎረቤቶቻችን ቅድሚያ እንሰጣለን። በዚህም ችግራቸውን ተጋርተን ለመፍትሔው አብረን መሥራት፣ ጸጋዎቻችንን በጋራ በማልማትና በመጋራት ተባብሮ ለማደግ ያለንን ራዕይና ጉጉት በተግባር ለመተርጎም ያስችላል። ህልውናችንን እና ሀገራዊ ጥቅሞቻችንን በአስተማማኝ ለመጠበቅና ለማራመድ የሚያስችል ዕድልም ይፈጥራል።
ሀገራችን በረጅም፣ በመካከለኛና በቅርብ ዘመን ታሪኳ የባሕር በር ባለቤት ነበረች።ከቅርንም ከሩቅም በተሸረበ ተከታታይ ሸፍጥ ተገፍታም የባሕር በሯን አጥታ ነበር። በኋላም በድጋሚ የባሕር በር ባለቤት ሆነች። በስተመጨረሻም ለሥስት ዐሥርተ ዓመታት በዘለቀና በውስጥ ቀውስና በውጭ ሤራ በታገዘው የእርስ በርስ ጦርነት ተካሄዷል።
በርስ በርስ ጦርነቱ ማብቂያ ላይም በሕግም በታሪክም ፊት በተፈጸመ ስሕተት የባሕር በር አልባ ሆና ላለፉት 30 ዓመታት ዘልቃለች። ይህንን የታሪክ ስብራትና የትውልድ ቁጭት ለማረም ባለፉት አምስት ዓመታት የለውጡ መንግሥት ከጦርነት በመለስና በሰጥቶ መቀበል መርሕ የሀገራችንን ቁመናና ዕድገት የሚመጥን ዘላቂና አስተማማኝ የወደብና የባሕር በር አማራጮችን ስለማስፋት ሲያውጠነጥንና ሲመክርም ሲሞክርም ቆይቷል።
በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ላይ ይኸው ሐሳብ ዳብሮ ለኢትዮጵያውያን እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይፋ የመንግሥት አቋም መሆኑ ተበስሯል። መንግሥት ይፋ ባደረገው ይኸው አቋሙ ከማንም ሀገር ጦርነት እንደማይገባና ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አማራጮች መኖራቸውን እንደሚያምን፣ ኢትዮጵያም ያሏትን ጸጋዎች ለመጋራት ዝግጁ መሆኗን ሲገልጽ ቆይቷል።
በዚሁ መሠረት ጆሮ መስጠት ለቻሉና ለፈለጉ ሁሉ አቋማችንን ለማስረዳት ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን።
ከሶማሊላንድ ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ጉዳዮች ለወራት በብስለትና በስክነት ምክክር እና ድርድር ሲካሄድ ቆይቷል። እነሆም ሁለቱንም ተጠቃሚ በሚያደርግ አግባብ የመግባቢያ ሰነድ ተፈርሟል።
ይኸው ሰነድ ለኢትዮጵያ በኤደን ባህረሰላጤ ላይ ዘላቂና አስተማማኝ የባሕር ኃይል ቤዝና ኮሜርሻል ማሪታይም አገልግሎት በሊዝ የምታገኝበትን ዕድል የሚያስገኝ ሲሆን መንግሥት አስቀድሞ ይፋ ባደረገው አቋሙ መሠረት ሶማሊላንድን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሊዙ የሚታሰብ ድርሻ እንዲኖራት ያስችላል።
ከዚያም ባሻገር በሂደት ሶማሊላንድ ዕውቅና ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት በጥልቀት አጢኖ አቋም የሚወስድበትን አግባብም ያካትታል።
ቀጣናችን የተቸረው ጸጋ ለሁላችንም ከበቂ በላይ ነው። በሥጋት ይሁን በክፋት ተሸብቦ ትብብርን መንፈግ በሕዝቦች ጉስቁልና የሚመነዘር ዝቅታን እንጂ የተሻለ ነገን ለመፍጠር አይቻልም። ከሶማሊ ላንድ ጋር የተደረገው ስምምነት መንግሥት የኢትዮጵያን መሻቶች ከጎረቤቶቿ ጋር በሚደረግ ትብብር፣ በሰጥቶ መቀበልና በሰላማዊ መንገድ ብቻ ለማሳካት ያለውን እምነት በተግባር ያሳየበት ነው። ይኸው ዕድል ለሁሉም ክፍት የነበረና ክፍት ሆኖም የሚኖር ነው።
ስምምነቱ የኢትዮጵያውያንን የዘመናት ጭንቀትና ቁዘማ ለማከም የሚያስችል አጋጣሚን የፈጠረ ነው። በመሆኑም ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያስደስት ታሪካዊ ክስተት ነው። ሁሉም ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንዲሁም የቀጣናው ሰላም የሚገዳቸው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አባላት ሁሉ ሊደሰቱ ይገባል።
በዚህ ስምምነት የሚጎዳ አካልም ሆነ ሀገር የለም። የተጣሰ ሕግና የተሰበረ እምነትም የለም። እውነታው ይኸው ቢሆንም ማንም እንደሚገምተው በዚህ አወንታዊ ድምዳሜ የሚከፋ፣ የሚደነግጥና ሁኔታውን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀስ አካል አይኖርም አይባልም።
በመሆኑም በተለይ ኢትዮጵያውያን በርግጥም ሀገራችን በመልኳና በቁመናዋ ልክ በቀጣናው፣ በአህጉራችንና በዓለም አደባባይ ተገቢ ሥፍራዋን ስታገኝ፣ ገንቢ ሚናዋን ስትወጣ፣ ጥቅሞቿንም ስታስከበር ብቻ በጋራ እንደምንከበር ማመንና ለዚህም ልዩነቶቻችንን ከመቼውም ጊዜ በላይ በማቻቻል ተያይዘን ከፍ እንል ዘንድ ይህን አጋጣሚ እንደንጠቀምበት የኢፌዴሪ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።
ይህ በዘመናት አንዴ የሚከሠት የታሪክ እጥፋት በመሆኑ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ሀገራችንን በጋራ እንታደግ!!
ከዘመናት በኋላ በታሪክ የማንወቀስ እንድንሆን ያለንበትን ምእራፍ ከመወራረፍና ከመጠላለፍ ተላቀን የኢትዮጵያችን ከፍታ ማብሠሪያ ለማድረግ በአንድነት አብረን እንትጋ!!
አዲስ አበባ
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
2016 ዓ.ም
0 Comments