የድሎቻችን ጠንካራ መሰረት የአመራሩ ቁርጠኝነት!




ፊንፊኔ ታህሳስ 28/2016(YMN)ኢትዮጵያችን በርካታ ድሎችን አስመዝግባለች ግን ደግሞ ችግር ውስጥ ናት፤ይህ እውነት ነው በድርቅ አደጋ ምክንያት የሚላስ የሚቀመስ ያጡ በርካታ ዜጎች አሉ፤የኑሮ ውድነቱ ሲታከልበት ሁላችንም ያለንበትን ሁኔታ እናውቃለን፤ችግሩ ተጨባጭ  ምክንያት ያለው ነው

የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግር ብለን በሁለት ከፍለን ልናየው እንችላለን፤ቀደም ሲል ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ ሰፈራቸው የሸሹት ትዕቢተኞች በትዕቢት ተወጥረው ተዘጋጅተውበት ሆን ብለው ከቅርብና ሩቅ ወዳጆቻቸው ጋር መክረውና ዘክረው የከፈቱት፤ለሁለት ዓመታትም የዘለቀው የሰሜኑ ጦርነት እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች ዜጎች ጥረው ግረው ኑሮአቸውን እንዳያሻሽሉና በአጠቃላይም የምርት አቅርቦት ችግር እንዲፈጠር እንቅፋት ሆነው ቆይተዋል፤ይህ ሰው ሰራሽ ችግር ነው፤ሰዎች የፈጠሩብን መከራ!

በሕዝብ ትግልና እምቢ ባይነት ከስልጣን የወረደው ኃይል ወደ ለመደው ስልጣን  ተገቢ ባልሆነ አካሄድ ለመመለስ ጥረት ባያደርግ ኖሮ የሰሜኑ ጦርነት አይቀሰቀስም፤ አሁን ያለው ሁኔታም አይፈጠረም ነበር

ጦርነቱ ከበዛው የለውጡ አመራር ገደብ አልባ ትዕግስት በኋላ ሲፈነዳና ምቹ ሁኔታ ሲገኝ የጦርነቱ ተዋናዮች በርካታ መሆናቸውን ተመልክተናል፤የውስጥና የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የሌለ መሆኑን ያለፈውን ሂደትና ውጣ ውረድ በትውስታ ወደ ኋላ ሄደን ከተመለከትን ስፍር ቁጥር የሌለው ነው

በጥቅም የተሳሰሩ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ምን ያላደረጉት ጥረት አለ?በኢትዮጵያችን ጉዳይ ላይ ከተጠራው አለም አቀፍ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተደጋጋሚ ስብሰባ ጀምሮ ያለው ኩነት ቢዘረዘር ማብቂያ የሌለው መሆኑ ይታወቃል

ጦርነቱ የእጅ አዙር ጦርነትም ነበርና የውስጥ አጋፋሪው ብዙ ድጋፍና እንክብካቤ ነበረው፤ከቴክኖሎጂ ሳታላይት መሳሪያዎች እስከ ኃይል ሰጪ ምግቦች አቅርቦትና ድጋፍ የተደረገለት እንክብካቤና እሹሩሩ የበረከተለት ነበር፤በመጨረሻም በኢትዮጵያ እምቢ ባይነት ሁሉም እፍረቱን ተከናንቦ ጭጭ ለማለት የተገደደ መሆኑን እንገነዘባለን

በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ምክንያት  ጦርነቱ  ቢጠናቀቅም የዜጎችን የኑሮ እንግልት ያበረከተው ሰው ሰራሹ ችግር ተስፋፍቶ እንዲቀጥል ሽንፈት ተከናንቦ በቁጭት የተንገበገበው የውስጥ ኃይል ከታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላት የግብጽ መንግስት ጋር ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር ያልተቋረጠ ጥረት አድርጓል

በኦሮሚያና አማራ ክልል ሸኔና  ሌሎች ታጣቂዎች በየአካባቢው የተፈለፈሉት በጦርነቱ የተሽመደመደው ኃይል በለመደው ሴራዊ አካሄድ ባደረገው ድጋፍና በፈጠረው ምቹ ሁኔታ ምክንያት መሆኑን መካድ አይቻልም

ሕወሃት በዋናነት ሸኔ ከሚባለው አሸባሪ ቡድን ጋር በመተባበር እንደሚሰራ በጦርነቱ ወቅት በአደባባይ ይፋ አድርጎ ነበር፤የአሸባሪው ሸኔ ቡድን አመራርም ከሕወሃት ጋር ስትራቴጂያዊ ስምምነት ያለው መሆኑን ይፋ በማድረግ የለውጡን አመራር ለማስወገድ ጥረት አድርጓል

አይበገሬው የለውጡ አመራር ግን ለሁሉም ፍንክች አላለም፤ሁለቱ ቡድኖች ሕወሃትና ሸኔ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ስምምነታቸውን እንዳልሻሩ ጋብቻቸውን እንዳልፈቱ ኋላ ላይ በኦሮሚያ የታየው የሸኔ ማንሰራራትና መፍጨርጨር ተጨባጭ ማስረጃ ይሆናል

በሌላ በኩል የሕወሃት ሰዎች ሙሉ በሙሉ እንዲወገዱለት ብርቱ ፍላጎት የነበረው የአንድነት ኃይል ነኝ ባዩ ባንዳም መጀመሪያ ላይ ለአመራሩ ያለውን ማንቆለጳጰስ ቢያበዛም ከለውጡ አመራር ጋር ያደረገው የስምምነት ፊርማ ያለ በሚመስል ሁኔታ “ተክደናል” በሚል ምክንያተ ባልተጠበቀ ፍጥነት የለውጡ አመራር ላይ ጣቱን መቀሰር ጀመረ

ይህ ቆሞ ቀር ጽንፈኛ ኃይል ቀደም ሲል በጦርነቱ ወቅት ውስጥ ለውስጥ በአማራ ክልል ያደራጀውን ጽንፈኛ በመተማመን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አባቶቻችን መቀመጫ አራት ኪሎ እንገባለን ሲል የሚታወቅበትን ፉከራና ቀረርቶ በማሰማት ድንፋታውን በአደባባይ ለሁሉም አሳየ

ጀግናው የለውጡ አመራር ለዚህም የሚንበረከክ አልሆነም!አመራሩ ከመነሻ ጀምሮ ፈተናው ቢበረክትበትም ተስፋ ባለመቁረጥ የኢትዮጵያ ስም በዓለም አዳባባዮች ላይ እንዲጠራ አድርጓል በህዳሴ ግድብ ግንባታና ውሃ ሙሌት የተጎናፀፍነው ድል፤በስንዴ ምርት የተመዘገበው ለውጥ፤በአረንጓዴ አሻራ ልማት የታጀበው የብሪክስ ስብስብ አባልነትና ሰሞኑን ለባህር በር ባለቤትነት ከሶማሌ ላንድ መንግስት ጋር የተደረገው ታሪካዊ የመግባቢያ ስምምነት ዋና ዋናዎቹ ተጨባጭ ድሎቻችን ናቸው

እነዚህ የሀገር ድሎች አመራሩ ጠንካራና ቁርጠኛ ባይሆን ኖሮ ሊታሰቡ የሚችሉ አይደሉም፤ለዘርፈ ብዙ ችግሮች እጅ ያልሰጠው የለውጡ አመራር በውስጡ የተሰገሰጉ የጠላት ደጋፊዎችም በሂደት ራሳቸውን እንዲያጋልጡ አድርጓል፤የውስጥ ሰርጎ ገብ ቦርቧሪዎች የአስመሳይነት ሁኔታ በቀጣይ የሚታይ ይሆናል

አሁን የሰላምና ፀጥታው ችግር በሂደት እየተቀረፈ ነው በማን አለብኝ የተዘጉ መንገዶች ሁሉ ሲከፈቱ የዜጎች ዝውወርና የምርት አቅርቦት ምቹ ሁኔታ የሚያገኝ ይሆናል፤ይህ እንዲሆን ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችንና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ቀጣይነት ያለው ስራ በመስራት ላይ የሚገኙ መሆናቸው ይታወቃል

በተፈጥሮ ችግር በዝናብ እጥረት ምክንያት በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች በተለመደው ሁኔታ የምግብ እህል ማምረት ባለመቻል በድርቅ አደጋ ምከንያት እርዳታ ለመሻት የተገደዱ በርካታ ዜጎቻችን ድጋፍ የሚያገኙ ይሆናል፤መንግስት አሁንም ባለው አቅም ለተቸገሩ ወገኖቻችን ድጋፍ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፤ይህም ሊሆን የቻለው ጠንካራ፤ቁርጠኛና ለሁሉም ችግሮች የማይበገር አመራር ስላለን እንደሆነ ይታወቃል!

@ጃርሶ ባላገሩ ከፊንፊኔ

 

 

 

Post a Comment

0 Comments