ቦኮ ሀራም በአማራ ክልል




በዚህ ዕውቀትና ሰብአዊነት በአደገበት ዘመን"እኔን ያየ ይቀጣ"የሚል የጭካኔ ፅሁፍ የተለጠፈበትንና በጭንቀት የተዋጠ ሰው ቪዲዮ የተመለአተ ሁሉ በሀዘንና በቁጭት አንድ ነገር ያስታውሳል-የናይጀሪያውን ጨካኝ ቡድን ቦኮሀራምን!!የአማራ ህዝብ የራሱን ቋንቋ በሚናገርና የራሱን ጥያቄዎች ቀምቶ ለዝርፊያና ለግድያ በሚጠቀም የአማራ ቦኮሀራም ቡድን ስቃይ እየደረሰበት መሆኑንም ይህ ጨካኝና ዘራፊ ቡድን የፈፀማቸውን ግፎች ሁሉ በማስታወስ ልቡ በሀዘን ይሰበራል።
ቪዲዮው የአማራው ቦኮሀራም ቡድን "ማረኩት"የሚለውን ኢትዮጵያዊ ዜጋ ጠመንጃ ደግኖ ተናገር ያለውን ሁሉ እንዲናገር ሲያስጨንቀውና ሲያስፈራራው ያሳያል።"ፋኖን በህዝብ ለማስጠላት ብልፅግና ልኮኝ ነው"እንዲል ያደርገዋል።"ስንት ሴት ደፈርክ?"የሚል ጥያቄ ያቀርብለትና"አልደፈርኩም"የሚል መልስ ሲሰጥ"ደፍሬአለሁ በል"የሚል ዛቻ ሲሰነዘርበት"አንድ ሴት ደፍሬአለሁ"ይላል።ድንቁርና በጭካኔ ሲታጀብ ወደጭራቅነት እንደሚያድግ የታየው ደግሞ"በማጥፋትህ በራስህ ላይ ምን ትፈርዳለህ?"የሚለው የአማራው ቦኮሀራም ቡድን አስጨናቂ ጥያቄና መልስ ነው።"የፈለጋችሁትን ወስኑብኝ"የሚል የፍርሀትና የጭንቀት መልስ ሲሰጥ "ራስህ በራስህ ላይ ፍረድ"ይሉታል።"ፋኖ ባለውለታዬ ስለሆነ ሞት ይገባኛል"አለ በዚህ አረመኔ ቡድን የሚዋከበው ዜጋ። በዓለም ላይ ተደርጎ በማያውቅ ጭካኔ ተገዶ በራሱ ላይ የሞት ፍርድ የፈረደው ይህ ዜጋ ከቪዲዮው ጀርባ ምን ዓይነት ግፍ እንደተፈፀመበትና "የሞት ፍርድ ይገባኛል"እንዲል የተደረገበት ጭካኔ በዓይነህሊና ሲታሰብ አዕምሮን ያስጨንቃል።
ይህ ጨካኝና ኋላቀር ዘራፊ ቡድን እንዴት ከናይጀሪያው አረመኔ ቦኮሀራም ጋር ሊመሳሰል ይችላል?የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል።የናይጀሪያው ቦኮሀራም በ2002(እ.ኤ.አ)በሰሜን ምስራቅ ናይጀሪያ የተመሰረተና በህቡዕ ንፁሀንን ሲገድልና አስተሳሰቡን ሲያስፋፋ ቆይቶ በ2009(እ.ኤ.አ)የትጥቅ ትግል መጀመሩን በይፋ ያወጀ እጅግ ፅንፈኛ ቡድን ነው።ዋነኛ የትጥቅ ትግል ስልቱም ግድያ÷እገታና ዝርፊያ ነው።እንደሌሎች አሸባሪ ቡድኖች እንደውም እጅግ በከፋ ሁኔታ በጭካኔውና በአረመኔነቱ የሚጠቀሰው ቦኮሀራም የተመሰረተበት ዓላማ ከሀይማኖት ገለልተኛ የሆነውን የናይጀሪያ መንግስት በኃይል ገልብጦ እስላማዊ መንግስት ለመመስረትና የሽያ እስልምናን አጥፍቶ የሱኒ እስልምናን "ንፅህና"ለመጠበቅ ነው።ቦኮሀራም የናይጀሪያ አንዱ ቋንቋ በሆነው ሀውሳ ቋንቋ "የምዕራባውያን ትምህርት ኃጢአት ነው"(Western education is a sin)የሚል ነው።በዚህ አስተሳሰቡም በናይጀሪያ ትምህርት እንዳይኖርና የናይጀሪያ ህፃናትና ወጣቶች እንዳይማሩ ይከለክላል።በት/ቤቶች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት በመሰንዘር ተማሪዎችንና አስተማሪዎችን ይገድላል÷ይጠልፋል።በዚህ አረመኔ ቡድን ከ300ሽህ በላይ ህፃናት ተገድለዋል።ከ2.3ሚሊዮን በላይ ህዝብ ከአካባቢው ተፈናቅሏል።ይህ ጨካኝ ቡድን ከናይጀሪያ አልፎ በካሜሩን÷ቻድ÷ኒጀርና ማሊ በመሳሰሉ የጎረቤት አገሮች ጭምር የሚንቀሳቀስ እንደመሆኑ የአካባቢዎቹ ህዝብ በምግብ እጥረትና በርሀብ እንዲሰቃይ ምክንያት ሆኗል።በዚህ ድንበር ተሻጋሪ የጭካኔ ድርጊቱ ምክንያት የአፍሪካ ህብረት በ2015(እ.ኤ.አ)የክልላዊ ሀገራት የጋራ ወታደራዊ ጥምረት ግብረኃይል (Regional Multinational Joint Task Force)በማቋቋም ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድበት አዟል።
የናይጀሪያው ቦኮሀራም በተለይ በት/ቤቶች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት በመሰንዘር÷ትምህርት እንዳይሰጥ በመከልከል÷ ተማሪዎችንና መምህራንን በመረሸንና በማገት ይታወቃል። በ2015(እኤአ)ቦርኖ በተባለው የናይጀሪያ ግዛት ቺቦክ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ት/ቤት ላይ ጥቃት ፈፅሞ ዕድሜአቸው ከ16-18 የሆኑና አብዛኞቹም የክርስትና ኃይማኖት የሚከተሉ 276 ልጃገረድ ተማሪዎች አግቶ ወደጫካ በመውሰዱ ዓለምን ማስጨነቁ አይዘነጋም።ልጃገረዶቹንም ለምግብ አብሳይነትና ለፆታዊ ፍላጎት ይጠቀምባቸው እንደነበር አይዘነጋም። የናይጀሪያ ሰራዊት በወሰደው ወታደራዊ እርምጃና ታጋቾቹም ከእገታ ለማምለጥ በአደረጉት ጥረት አብዛኞቹ ቢለቀቁም 100ያህል ልጃገረድ ተማሪዎች ሁኔታ እስካሁን አልታወቀም። እነዚህ ተማሪዎች ሳይሞቱና ሳይገደሉ እንዳልቀረ ይታመናል። ከዚያም በፊት ዩቤ በተባለው የናይጀሪያ ግዛት በአንድ ት/ቤት ላይ በፈፀመው ጥቃት ከ42በላይ ተማሪዎች መግደሉ ይጠቀሳል።
የአማራው ቦኮሀራምና የናይጀሪያው ቦኮሀራም በአብዛኛው የሚመሳሰሉት በአስተሳሰብ ኋላቀርነታቸው÷በጭካኔአቸውና በትጥቅ ትግል ስልታቸው ነው።ልክ እንደናይጀሪያው ቦኮሀራም የጎጃሙ ቦኮሀራም በቅርቡ ለቀን ሰራተኛነት ወደህዳሴ ግድብ ይጓዙ የነበሩ 275 የደቡብ ኢትዮጵያ ልጆችን አግቶ መግደሉና ማሰቃየቱ በቅርብ ጊዜ ማስረጃነት ይጠቀሳል።ልክ እንደ ናይጀሪያው ቦኮሀራም የአማራው ቦኮሀራም ቡድን የአማራ ልጆች እንዳይማሩ ይከለክላል÷አስተማሪዎችን በእንብርክክ እያስኬደ ሲያዋርድ÷ት/ቤት ከተከፈተ እርምጃ እወስዳለሁ እያለ ሲፎክርና ሲያስፈራራ ታሪክ መዝግቦታል።የአማራው ቦኮሀራም ልክ እንደናይጀሪያው ቦኮ ሀራም የአማራ ህዝብ አርሶና ነግዶ እንዳይኖር÷ክልሉ እንዳይለማ በማወክ የምግብ እጥረትና ርሀብ እንዲከሰት አድርጓል።ለገበሬ የሚቀርብን ማዳበሪያ ሳይቀር እየዘረፈና እንዳይሰራጭም እየከለከለ የአርሶአደሩን የእርሻ በሬ ሳይቀር አርዶ እየበላና ህዝብ እየዘረፈ ድህነትን አስፋፍቷል።ልክ እንደናይጀሪያው ቦኮሀራም ንፁሀን ዜጎችን እያገተና ሴቶችን እየደፈረ ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል ፈፅሟል።የአማራው ቦኮሀራም የአማራ ህዝብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲታወክና ድህነት እንዲስፋፋ አድርጓል።በዚህ ዘራፊና ጨካኝ ቡድን ኋላቀርና ነውረኛ የጭካኔ ድርጊት ምክንያት የታላቁና የአገር ወዳዱ የአማራ ህዝብ ክብር ክፉኛ ተዋርዷል።ይህ ጨካኝና አረመኔ ቡድን በባዕድ የተገዛና ከኋላም ህወኃት የሚያሽከረክረው የአማራ ህዝብ ጠላት ስለመሆኑ አሁን ከምንጊዜውም በበለጠ ገሀድ ሆኖአል።ህወኃት ኢትዮጵያን ለማፍረስና አማራን "ለመበቀል"በዘመተበት ወቅት "ጀግና በለውበለው"ሲሉ የነበሩ የህወኃት የሚዲያ ፕሮፓጋንዲስቶች እነ እስታሊን ገብረስላሴና እነአሉላ ሰለሞን "ፋኖን ወጥረን እንደግፋለን"እያሉን ነው።አዎ ድሮም በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ይህን ዘራፊ ቡድን ወጥረው ይደግፉት እንደነበር እናውቃለን።የአማራ ህፃናትና መነኩሴዎች በህወኃት ወራሪ ኃይል ሲደፈሩና የአማራ ህዝብ ህይወትና ንብረት በጦርነት ሲወድም ከበሮ ይደልቁብን የነበሩት የህወኃት ፕሮፓጋንዲስቶች ዛሬም የአማራ ህዝብ መከራ እንዲራዘም እየወተወቱ ነው።የዚህ ድጋፍ አንደምታ ግልፅ ነው።"የማን ቤት ፈርሶ የማን ሊበጅ"ነው ነገሩ።አማራን በራሱ ልጆች ማደህየትና አቅመቢስ ማድረግ ከዚያም የሚፈልጉትን መሬት ይዘው ኢትዮጵያን በማፍረስ የትግራይን ሪፐብሊክ መመስረት ነው ምስጢሩ።
የዚህ ዘራፊ ቡድን ቃል አቀባዮችና የፕሮፓጋንዳ ልሳኖች ማንነታቸው ተጋልጦ "ህወኃትና ፋኖ አብረው እንዲሰሩ"እሰበኩ ነው።ከዚህ በላይ ከሀዲነት ከዚህ በላይ የአማራና የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላትነት ከወዴት እንደሚገኝ አላውቅም።
እንደአንድ የክልሉ ተወላጅ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የፌዴራሉንና የአማራ ክልልን መንግስት የምጠይቀው ጥያቄ አለኝ።አንደኛው በአማራው ቦኮሀራም የጭካኔ ድርጊት "በራሱ ላይ ሞት እንዲፈርድ"የተገደደው ዜጋ እንዲሁም አስተማሪዎችን ሴቶችን በጉልበታቸው ማስኬድን ጨምሮ ሌሎቸ ዜጎች የት እንደደረሱ እንዲከታተሉና የአማራው ቦኮሀራም የግፍ ሰለባዎች ፍትህ እንዲያገኙ እጠይቃለሁ።በነዚህ ዜጎቻችን ላይ ግፍ የፈፀሙ አረመኔዎች "በሰላም እጃቸውን ሰጡ"በሚል ሽፋን ከህግ ተጠያቂነት የሚያመልጡ ከሆነ በታሪክም በትውልድም የሚያስወቅስ ይሆናል።
ሁለተኛ በውጭ አገርና በውስጥም ሆነው የዚህ ኋላቀርና ዘራፊ ቡድን ቃል አቀባይና የፕሮፓጋንዳ ልሳን የሆኑ የደም ነጋዴዎችና የዩቲዩብ ጡረተኞች ቢያንስ ከታሪክ ፍርድ እንዳያመልጡ አስፈላጊው ሁሉ እንዲደረግ እጠይቃለሁ።በንፁሀን ደምና በአማራ ህዝብ ጉስቁልና ሀብት ያካበቱ የደም ነጋዴዎች ሀብት ተጠንቶ እርምጃ መወሰድ ይኖርበታል።የጎጃሙ ቦኮሀራም መሪ ነኝ የሚለው ዘመነ ካሴና ጓደኞቹ ከፍተኛ ብርና እያንዳንዳቸው ከሁለት ያላነሰ ህንፃ እንዳላቸው የታወቀ ነው።የወሎና የሸዋ ቦኮሀራም ቡድን መሪ ነን የሚሉትም በደም ያካበቱት ሀብት አላቸው።በውጪ የሚገኙት የደም ነጋዴዎችና የዩቲዩብ ደሞዝተኞች በሀገር ውስጥ ቤትና ንብረት እንዳላቸው ይነገራልና መንግስት እርምጃ እንዲወስድ እጠይቃለሁ።የደም ነጋዴዎች በንፁሀን ደም ነግደው መቅረት የለባቸውም።

በዓለምነህ አበበ

Post a Comment

0 Comments